If You a returning customer
Sign In
Password forgotten? Click here.
If You a new customer
By creating an account at Tsehai Publishers you will be able to shop faster, be up to date on an orders status, and keep track of the orders you have previously made.
Continue
Click to enlarge
Gobena A Military and Political Life ጎበና: ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት (1810-1881)
Price : $29.95
Add to Cart Add to wish list
ይህ መጽሐፍ በአራት ክፍሎችና በዓሥራ አራት ምዕራፎች ተዋቅሮ ክፍል አንድ ከዋናው የታሪክ ዳሰሳና ትንተና በፊት ታሪካዊውን ዳራ ለመተረክ ይሞክራል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ጎበና ሊደርስ ከቻለበት የወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ የእውቅና ጣርያ ድረስ ያለፈባቸውን በፈተና የተሞሉ፣ የዚያኑ ያክል በውጤት የታጀቡ የሕይወት ልምዶቹን ለመዳሰስ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን፤ ሦስተኛው ከዚሁ ተያያዥ በሆነ መልኩ ጎበና የተጎናጸፈውን እውቅና እንደምን አድርጎ ሀገራዊ ፋይዳ ወደአለው ነገር እንደለወጠ ለማሳየት ይጥራል። ክፍል አራት የጎበና የመጨረሻ ዘመናት ያለ አቻ ወራሽ ሲጠናቀቁ የኦሮሞ ሕዝብ የተጋረጠበትን ከሀገርና ከመንግሥት ባለቤትነት የመንሸራተት ፈተና ለምን እንደተከሠተ ለማመላከት ጥረት ያደርጋል።
በዝርዝር ምዕራፎቹ ስለ ጎበና እስከ አሁን የነበሩትን የተለያዩ እይታዎችና አመለካከቶች፣ ከጎበና መወለድ በፊት በዓሥራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን መጀመሪያና በልደቱ ወቅት የጎበና የትውልድ ቦታ በነበረው ሰሜን ሸዋ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በይበልጥ ደግሞ የኦሮሞና ዐማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች ጎበናን እንዴት እንደቀረጹት፣ የጎበናን ልደት፣ ልጅነትና ወጣትነት እንዲሁም የሎሌነት፣ የአማችነት እና ደጅ አጋፋሪነት በመጨረሻም የሽፍትነት ጊዜውን፣ የግዛት መስፋፋትና የሰፊውን ኢትዮጵያ ሀገር የመመሠረት ውጥንና ከምኒልክ ጋር መተዋወቁን ይገልጻል።
ጎበና የተለያዩ ሹመቶችን ለምሣሌ የደጃዝማችነትና ከዚያም የራስነት ሹመትና ማዕረግ ላይ እንዴት እንደደረሰና በተለይም የጦር አበጋዝነትን ያክል ትልቅ ሃላፊነት አንዴት እንደወሰደ በተጓዳኝም “የግዛት ማስፋፋትና ሀገር ማቅናት” ስተራቴጂ እንዴት በጋራ እንደተነደፈ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ መሪዎች እንደተተገበረ ይተርካል። በመጨረሻም ጎበና ብዙዎቹን የቤት ሥራዎቹን ቀድሞ በማጠናቀቁና ሌሎቹን ባለድርሻ አካላት ድንክዬ በማድረጉ በምኒልክ ዙሪያ ባሉ ሰዎች ጉትጎታና ማጉረምረም በመጀመሪያው ስምምነት መሠረት ሳይሆን ውጤቱን በማጠፍ ጎበና ያስገበራቸውን አካባቢዎች ሌሎች እንደ ተሾሙበት፣ የጎበናን ሃይማኖታዊ ክንውንና የአብያተክርስቲያናት ግንባታ እንቅስቃሴ እንዱሁም ቤተሰባዊ ሕይወቱን በተለይም ጋብቻና ልጆች፣ ሞትና አሟሟቱን በተመለከተ ማስረጃ እስከፈቀደ ድረስ ተገልጾ በመዝጊያውም ስለጎበና የተነገረው ነገር ያለውን አንድምታ በጸሐፊው ግንዛቤ ልክ የማሰሪያ ሐሳብ የተሰጠበት መጽሐፍ ነው።
ዕውቅና
መቅድም
ክፍል አንድ፡ የጥናቱ ዳራ
ምዕራፍ አንድ፡ መንደርደሪያ
ምዕራፍ ሁለት፡ ሸዋ በጎበና የልደት ዘመን
ክፍል ሁለት፡ ፈታኝ የዕድገት መሰላል (1810-1870)
ምዕራፍ ሦስት፡ የጎበና የልጅነትና የወጣትነት ዘመን
ምዕራፍ አራት፡ የሽግግር ዓመታት
ምዕራፍ አምስት፡ የጎበና የጦር አበጋዝነት ሹመት
ክፍል ሦስት፡ ወርቃማ ዓመታት (1870-1878)
ምዕራፍ ስድስት፡ የጎበና “የቱለማ ኮንፌደሬሲ” ምሥረታን ማጠናቀቅ
ምዕራፍ ሰባት፡ የጎበና የደቡብ መጫና የከፋ ዘመቻ
ምዕራፍ ስምንት፡ የጎበና የሰሜን መጫና የአንፊሎ ዘመቻ
ምዕራፍ ዘጠኝ፡ የጎበና የአርሲ ዘመቻ
ምዕራፍ አስር፡ የጎበና የ“ዓረብ” ዘመቻ
ምዕራፍ አስራ አንድ፡ የጎበና የጉራጌ ዘመቻ
ክፍል አራት፡ ሲያልቅ አያምር (1878-1881)
ምዕራፍ አስራ ሁለት፡ የታጠፉ የአጋርነት ስምምነቶችና ውጤታቸው
ምዕራፍ አስራ ሦስት፡ ጎበናና ክርስትና
ምዕራፍ አስራ አራት፡ የጎበና ቤተሰባዊ ሕይወት፣ ሞትና አሟሟት
መደምደሚያ
ዋቢ ጽሑፎች
መጠቁም
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በርካታ መጻሕፍትን ያዘጋጁ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የውጭ ዜጎች ወይ በማድበስበስ አልያም ሆነ ብለው በመዝለል የራስ ጎበና ዳጪን የሕይወት ታሪክና ዘመናዊት ኢትዮጵያን በመመሥረት የነበራቸውን ታላቅ ሚና ትኩረት ሳይሰጡት ቆይተዋል። ዶ/ር ደቻሳ አበበ ይህን የታሪክ ዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የተሳካለት ሥራ ሠርቷል። ይህ ሥራ በጥልቀት የተዘጋጀና በጉዳዩ ላይ በርካታ አዳዲስ መረጃዎችን ለአንባቢዎች ያቀረበ በመሆኑ እስከ ዛሬ በጉዳዩ ላይ የነበረውን የተዛባ ግንዛቤ ለማረም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። በመሆኑም አንባቢዎች ከዚህ መጽሐፍ ሰፊ ታሪካዊ ዕውቀትና ግንዛቤ እንደሚያገኙ አንዳች ጥርጣሬ የለኝም።
—ዶ/ር ተሰማ ተኣ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር
ራስ ጎበና ዳጪ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ከመሠረቱት ታላላቅ መሪዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ። በሸዋ ዐማራና ኦሮሞ መስተጋብር ፈጥረው ወደ ሀገር ግንባታ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ከአጼ ምኒልክ ጋር በዕውቅና የሠሩ እጅግ የተዋጣላቸው የጦር መሪም ነበሩ። ከ1960ዎቹ ጀምሮ የመገንጠል ዝንባሌ የነበራቸው ዋልታ_ረገጥ ፖለቲከኞች ስማቸውን ለማጉደፍ ቢሞክሩም የሕይወት ታሪካቸውን እውነተኛ ገጽታ በመተንተን ዶ/ር ደቻሳ የክብር ታላቅ ስፍራ ላይ መልሶ ያስቀምጣቸዋል። ራስ ጎበና ቢያልፉም እሳቸው ያሰለጠኗቸው የጦር መሪዎች (እንደነ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መኮንን እና ሌሎችም) ጣልያንን በማሸነፍ ድል ሊቀዳጁ በቅተዋል። ሀገርም ከቅኝ አገዛዝ ሥር ሳትወድቅ ነጻነቷን ጠብቃ ለሚቀጥለው ትውልድ ለመተላለፍ በቅታለች። ይህ እጅግ ተነባቢ የሆነ መጽሐፍ በሁሉም አንባቢ እጅ መግባት ያለበት ወቅታዊና አስፈላጊ መጽሐፍ ነው።
—ዶ/ር አየለ በከሬ፣ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ጥናትና ምርምር ማዕከል የታሪክ ፕሮፌሰር
ራስ ጎበና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ታላቅ ሚና የተጫወቱ የተከበሩ የፖለቲካ ሰውና የጦር መሪ ቢሆኑም በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጣቸው ቆይቷል። ይባስ ብሎ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኝ ልሂቃን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ሲሉ የራስ ጎበናን ታሪክ በማዛባት፣ ወጣቱ ትውልድ የእኝህን የሀገር ባለውለታና ብሔራዊ ጀግና እውነተኛ ታሪክ ሊረዳ አንዳይችል አድርገዋል። ይህ የዶ/ር ደቻሳ መጽሐፍ አንባቢያን ቀደም ሲል ስለራስ ጎበና ያነበቧቸውንና የሰሟቸውን የሀሰት ትርክቶች ቆም ብለው እንዲመረምሩ ለመርዳት ካለው ጠቀሜታ ባሻገር፣ የዓሥራ ዘጠነኛውን መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ለመረዳት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
—ዶ/ር ተፈሪ መኮንን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር
ዶ/ር ደቻሳ አበበ በጥቅምት 3፣ 1967 ዓ. ም በሰሜን ሸዋ ሳያደብርና ዋዩ ወረዳ ሳክላ አቦ የገጠር ቀበሌ ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በደነባ አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃውን በእነዋሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የመጀመሪያ ድግሪውን ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በታሪክ መምህርነት በ1991 ዓ. ም፣ የማስተርስ ድግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ በ1995 ዓ. ም እና ከኢንድራጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂ በ2001 ዓ. ም ያገኘ ሲሆን በታሪክ የትምህርት ዓይነት ደግሞ የዶክትሬት ድግሪ በ2008 ዓ. ም ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል።
ዶ/ር ደቻሳ በጋምቤላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ መምህርነት ያገለገለ ሲሆን አሁን በዚያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል በመምህርነትና በተመራማሪነት በማገልገል ላይ ይገኛል። በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በርካታ የጥናት ወረቀቶችን በተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚገኙ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትሟል።
View All Products
View All Authors
Sign up for our newsletter
Subscribe
Copyright © 2024 Tsehai Publishers All Rights Reserved.