Us and the Revolution [978-1-59907-078-0]

$34.95 $29.96



Author : Fikre-Selassie Wogderes



ISBN Code : 978-1-59907-078-0
Language : AMHARIC
Pages number : 454
Format : Paperback; 6"x9"; Illustrator

በጡረታ እስከተገለልኩበት ጊዜ ድረስ አብዮቱን በግምባር ቀደምትነት ከመሩት የደርግ አባላት ውስጥ አንዱ ነኝ። ደርግ ከመመሥረቱ በፊት በአገራችን የተካሄዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምን ይመስሉ እንደነበር፣ ደርግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ፣ ፖለቲካዊ ሥልጣንም እንዴትና ለምን ሊይዝ እንደበቃ፣ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ደግሞ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ በማምጣት አገራችን ከኋላ ቀርነትና ከድህነት ተላቅቃ የሠለጠነችና የበለጸገች እንድትሆን ያደረገውን ጥረትና የከፈለውን መስዋዕት በቅርብና በዝርዝር አውቃለሁ። በነበረኝ ሥልጣን ምክንያት ከሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለነበረኝ በየትኛውም አካባቢና መሥሪያ ቤት የተከናወኑ ሥራዎችንና የተፈፀሙ ስህተቶችን ከሞላ ጎደል አውቃለሁ።
 
በዚህ የተነሣ የደርግን ታሪክ የመፃፍ ሃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል። ከእሥር ቤት ከወጣሁ በኋላ አሁን ያለውና በተከታታይ የሚመጡት ትውልዶች የታሪካቸው አካል ስለሆነው የደርግ ታሪክ በከፊልም ቢሆን እንዲያውቁ የተወሰኑ ጉዳዮችን ብቻ የሚተርክ ይህን መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ። መጽሐፉ በጥድፊያ ሳይሆን በጥንቃቄና በጥልቀት መነበብ አለበት የሚል እምነት አለኝና መልካም ንባብ።
 
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ
የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር

“...በሊቀመንበርነት ስብሰባውን የሚመሩት ጄነራል ተፈሪ “የቋሚ ኮሚቴው በዛሬው ቀን የሚወያይበትን ጉዳይ አስመልክቶ የመቶ አለቃ ዓለማየሁ የደርጉ ዋና ፀሐፊ ይገልጽልናል” ብለው ስብሰባው መጀመሩን ካበሰሩ በኋላ ዓለማየሁ በአጀንዳው ላይ አጭር ገለጣ ማድረግ ሲጀምር ስልክ ተደወለ። ስልኩ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ አጠገብ ስለነበር ወዲያው ቅጭል እንዳለ መነጋገሪያውን በማንሳት ሃሎ አሉ። ከሌላው ጫፍ ማን እንደደወለ አላወቀንም። በኋላ እንደታወቀው ሌ/ኮሎኔል ዳንኤል ነበር የደወለው። ምን እንደተነጋገሩ አልተሰማም። ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ብቻ “እሺ እሺ” ብለው ስልኩን ዘጉት። ስልኩን እንደዘጉ “ይቅርታ ስልኩ የተደወለው ከጎንደር ነው። ጎንደር ውስጥ ችግር አለ። እናንተ ቀጥሉ” ብለው ከጀርባቸው ባለው በር በኩል ውልቅ አሉ። በዚህን ጊዜ ዓለማየሁና ሞገስ ጥርጣሬ የገባቸው መሰለ።

ዓለማየሁ ንግግሩን አቋርጦ በመስኮት በኩል ውጭ ውጭዉን መመልከት ጀመረ። ዓይኖቹ አላርፍ አሉ። ግራና ቀኝ ይመለከታል። አጠገቡ ያሉትን ሰዎች ሁሉ በጥርጣሬ ተመለከተ። ሻምበል ሞገስም በር በሩን ይመለከታል። ከአሁን አሁን አንድ ችግር ይከሰታል የሚል ፍርሃት ያደረበት ይመስላል። ሁሉም የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ፈርተዋል። እንደፈሩት አልቀረም ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ከወጡ ሁለት ደቂቃ እንኳን አልሞላም ከበስተጀርባ ባለው ኮሪደር የወታደሮችን እርምጃ ሰማን። ወታደሮች ሲንቀሳቀሱ በፊት ለፊታችን ባሉት መስኮቶች በኩል ተመለከትን። በዚህን ጊዜ ፍስሐ ደስታ “ተከብበናል” አለ። ወዲያው ሁለቱም በሮች በኃይል ተበረገዱ። ሁላችንም ደነገጥን፣ ቀልባችን ተገፈፈ፣ እጢአችንም የወደቀ መሰለን። ድርቅ ብለን በተቀመጥንበት ቀረን።...”

Close window