The Revolution and My Reminiscence [978-1-59907-108-4]

$44.95



Author : Fisseha Desta



ISBN Code : 978-1-59907-108-4
Language : Amharic
Pages number : 598
Format : Paperback

የኢትዮጵያ አብዮት ሰፊ፣ ፈጣንና ውስብስብ የነበረ ቢሆንም በግሌ ተካፋይ የነበርኩበትን፣ በዓይኔ ያየሁትንና በማስረጃ ያረጋገጥኳቸውን እውነታዎችን በተቻለ መጠን ከወገናዊነት በፀዳ መልኩ በዚህ መጽሐፍ ለማቅረብ ሞክሬአለሁ። የኔ ምኞትና ፍላጎት እኩልነት፣ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ አንድነቷና ልዑላዊነቷ የተጠበቀና የበለጸገች አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ዓላማ በመንደር ልጅነት፣ በጎሳና በዘር የሚለወጥ አይደለም። በዚያ የአብዮት ወቅት የተጋረጠብኝን ሴራና ተንኮል በመቋቋም፤ የገባሁትን ቃል ኪዳንና መሃላ ጠብቄ በንጹህ ህሊናና ቅንነት ሃገሬንና ሕዝቤን አገልግያለሁ። ደርግ በወሰዳቸው በጎ እርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ፤ በማወቅ፣ በድፍረት፣ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ፤ ሙሉ ሃላፊነትን በመውሰድ፤ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

የሰው ልጅ በተለያየ ምክንያት ለተለያየ ተፅእኖ መውደቁ ስለማይቀር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለራስ በማድላት ፍፁም ከወገናዊነት የፀዳ አይሆንም። እኔም ሙሉ በሙሉ ከወገናዊነት ውጭ ነኝ ብዬ ስለማላምን አንባብያን ይህንን በቅን ልቦና እንዲወስዱልኝ እጠይቃለሁ። ከሰው ስህተት አይጠፋምና መጽሐፉን በሚገባ አንብበው በጭፍን ሳይሆን በገምቢ መልኩ የሚሰጡትን ማንኛውንም አስተያየትና ሂስ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።

ፍሥሐ ደስታ (ሌ/ኮሎኔል)

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ም/ፕሬዝዳንት

“…ኮ/ል መንግሥቱ ጠመንጃቸውን እንዳነገቱ ብቅ ብለው በደንብ ከተመለከቱን በኋላ “ትክክል ነው” ብለው ተመለሱ። የመጡትም ቀደም ብለው ማን መቅረት ማን መገደል እንዳለበት በወሰኑት መሠረት ስህተት እንዳይፈጠር ለማረጋገጥ እንደነበር ግልፅ ነው።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ መጀመሪያ ወደነበርንበት የስብሰባ አዳራሽ ተጠራን። ወደዚያ ስናመራ ኮ/ል ተስፋዬ ገብረኪዳንን “ባለፈው ጄኔራል አማን ተገደሉ አሁን ደግሞ ሥራቸውን ከሚሰሩበት ቦታ አምጥተን፣ ራሳችን ሾመን እንዴት እኒህ ሽማግሌ [ጄነራል ተፈሪ] ይገደላሉ? ስለዚህ ለመንግሥቱ እንንገራቸው” አልኩትና ተያይዘን ወደቢሯቸው ገባን።

እኛም የመጣንበትን ስንነግራቸው “እውነታችሁን ነው” በማለት የውስጥ ስልክ አንስተው ከደወሉ በኋላ መነጋገሪያውን እያስቀመጡ “አዝናለሁ ጓዶች አልቋል” ብለው ነግረውን እያዘንን ወደ ስብሰባው አመራን። እንደገባን ኮ/ል መንግሥቱ መጥተው “ስለሁኔታው ለጦሩ ማስረዳት ስላለብኝ ኮ/ል ተስፋዬ ገብረኪዳን ከኔ ጋር እንድትሄድ” በማለት ጠየቁ። ኮ/ል ተስፋዬም “በማዛቸው ወታደሮች ፊት እጄን ሰቅዬ ወጥቼ ጦሩን ለማነጋገር ፈጽሞ ሕሊናዬ ሊቀበለው ስለማይችል አልሄድም፤ እንደውም ወደክፍሌ እመለሳለሁ” አለ። እኔም “ከእንግዲህ በዚህ ዓይነት እዚህ ግቢ ለመሥራት ፍላጐት የለኝም እኔም እንደተስፋዬ ወደክፍሌ መመለስ እፈልጋለሁ” አልኩ። መንግሥቱም ሽጉጣቸውን በማውጣት “ይህን እርምጃ ባልወስድ ኑሮ ሁላችንም አልቀን ነበር፤ በድያችሁ ከሆነ ግን ግደሉኝ” በማለት ሽጉጡን ጠረጴዛው ላይ ወረወሩት…”

Close window