Me and the Revolution [978-1-59-907804-5]

$34.95



Author : Fikre-Selassie Wogderes



ISBN Code : 978-1-59-907804-5
Language : Amharic
Pages number : 430
Format : Paperback

“እኔና አብዮቱ” መጽሐፍ ከታሪኬ መጨረሻ ገደማ ተነስቶ የተወሰኑ ኩነቶችን በመተረክ ይጀምርና ወደኋላ በመመለስ ስለትውልዴና አስተዳደጌ፣ ስለትምህርት ቤት ሕይወቴ፣ በሥራ ዓለም ቆይታዬና በኢትዮጵያ አብዮት ስለነበረኝ ተሳትፎ ይተርክና ግለ ታሪኬን መተረክ ያቆማል።
 
እኔ እውቅና ያገኘሁት በአብዮቱ በነበረኝ ተሳትፎ ስለሆነ ከአብዮቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጥቂት ሥራዎቼን በመጽሐፉ ጎላ ብለው እንዲታዩ አድርጌአለሁ። ከነዚህ ውስጥ ሊቀመንበሩ ወይም እኔ በመራናቸው በርካታ ስብሰባዎች ላይ ያሳለፍናችው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ወታደራዊ ውሳኔዎች የታሪኬ አካል በመሆናቸው ብቻ የተወሰኑትን መርጬ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጌአለሁ። በአብዮቱ ንቁ ተሳታፊ ከመሆኔም ባሻገር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ስለነበርኩ በርካታ ባለጉዳይ ግለሰቦችን እያነጋገርኩኝ መንግሥታዊና ግላዊ ውሳኔዎች ሰጥቻለሁ። በአገር ውስጥ ክፍለ ሀገራትን አውራጃዎችንና ወረዳዎችን እንዲሁም መሥሪያ ቤቶችን እየጎበኘሁና ነዋሪውን ሕዝብ ወይም ሠራተኞችን እያነጋገርኩና እያወያየሁ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቻለሁ፣ ትዕዛዞችንም አስተላልፌአለሁ። በውጪ አገሮችም ጉብኝት እያደረግሁ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ስምምነቶችን ተፈራርሜአለሁ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ፣ ወደ መጨረሻ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ በሠራሁባቸው ዓመታት ውስጥ ሚኒስትሮችን እየሰበሰብኩ በርካታ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን አውጥተናል። ከዚህ በላይ የጠቃቀስኳቸው ሥራዎች ስለመንግሥታችን ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜ የመንግሥት ሥራ ተደርገው ይጠቀሳሉ። የእኔን ግለ ታሪክ በምጽፍበት ጊዜ ግን የእኔ ታሪክ አድርጌ እወስዳቸዋለሁ። ስለሆነም በዚህ የግል ታሪኬን በሚያወሳው መጽሐፍ ውስጥ ጥቂቶቹን አካትቻለሁ።
 
ፍቅረሥላሴ ወግደረስ
የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር

“ደብዳቤዎቹን ካነበብኩኝ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ ጎን ጣል አድርጌ ከልጆቼ ጋር ማውራት ጀመርን። ነገሩን ችላ ብዬ የቀረበልንን ምግብ ለመቀማመስ ሞከርኩ፤ በትግል ጥቂት ቀማምሼ ተውኩት። ባለቤቴ ሐረገወይን ደስታ በፊቴ ላይ ለየት ያለ ሁኔታ የተመለከተች መሰለኝ ደብዳቤው ጥሩ ነገር እንዳልያዘ ጠርጥራለች፣ በደብዳቤው ምክንያት ነገር እንደገባኝም ገምታለች። እራታችንን ከበላንና ልጆቹን ካስተኛች በኋላ “ምነው ምን ሆነሀል? የተከፋህ መሰልከኝ” ብላ አትኩራ ተመለከተችኝ። እንዴት እንደማስረዳትና እንደማረጋጋት ለጥቂት ጊዜ ካሰላሰልኩ በኋላ “እንግዲህ ወሳኝና አሳሳቢ ጊዜ መጥቷል። ከዚህ በኋላ ጠንክሮ መገኘት አስፈላጊ ነው። ከነገ ጀምሮ ከሥራ ተባርሬአለሁ። ስለሆነም የሚመጣውን በፀጋ መቀበል ይኖርብናል” ብዬ ደብዳቤዎቹን እንድታነባቸው ሰጠኋት። ስታነብ ትኩር ብዬ እመለከታታለሁ። በየሴኮንዱ ፊቷ ይለዋወጣል። በጣም ደነገጠች። ለደቂቃዎችም አልተናገረችም፤ ፀጥ ብላ እየተመለከተችኝ ከቆየች በኋላ “ለመሆኑ አነጋግረውሃል? አስረድተውሃል?” እያለች አከታትላ ጥያቄዎች አቀረበችልኝ። “ስለውሳኔው ምንም የነገሩኝ ነገር የለም። ደብዳቤውን ሳነብ ነው የሆነውን የተረዳሁት [አልኳት]።”

Close window